Cinque Terre

Cinque Terre

መንፈሳዊ ላቦራቶሪ /የምክር አገልግሎት/ ያለው ጠቀሜታ

        ለመሆኑ መንፈሳዊ ላቦራቶሪ ማለት ምን ማለት ነው? መንፈሳዊ ላቦራቶሪ ማለት መንፈሳዊ ሕይወታችን ምን እንደሚመስል ዉስጣችንን የምናይበት የምክር አገልግሎት ነዉ። ይህ መንፈሳዊ ላቦራቶሪ በመካሪና በተመካሪ መካከል በሚኖረው የጥያቄና መልስ የግል ውይይት ነፍሳችን ያላትን ጥንካሬ እና ድክመት ለማየት ያስችላል። ሥጋችን በየሰዓቱ ምግብ እንደምንመግባት ሁሉ ነፍሳችንም ምግብ ያስፈልጋታል። ስለዚህ የነፍስ ምግብ የሆኑትን እንደ ፆም፣ ፀሎትና ስግደት በሥርዓት እናካሂዳለን? ቅዳሴ እናስቀድሳለን? ንስሃ ገብተን ነፍሳችንን ቅዱስ ቁርባን እንመግባታለን? እንደዚህም ሕይወታችን ከኃጢአት ርቃ የተለያዩ የፅድቅ ሥራዎችን በመሥራት ምን ያህል ነው በጥሩ ክርስቲያናዊ ስነ ምግባር የታነፀችው? እነዚህምንና ሌሎች ጠቃሚ የምክር ሓሳቦችን በማንሣት አጥጋቢ ምክርን በማግኘት ይህ መንፈሳዊ ላቦራቶሪ ሕይወታችንን የምንለውጥበት ታላቅ ዘዴ ነው።

        በሳይንሱ ዓለም የላቦራቶሪ መሣሪያ ተጠቅመን ዉስጣዊ አካላችንን በመመርመር ያለዉን ችግር ልናዉቀዉ እንችላለን። ሆኖም ግን በነፍሳችን ዉሰጥ ያለዉን ችግር ልናዉቀዉ አንችልም። ብዙ ጊዜ ሰዎች ትልቁ ችግራችን ነፍስ የምትባለዉ ታላቅ ሕይወት ተሸክመን የነፍሳችንን ችግር አለማወቃችንና ለማወቅም አለመጣራችን ነዉ። ምክንያቱም ሰዉ የተባለዉ ፍጡር ነፍስና ሥጋ የተባሉ ሁለት አካላት ተሸክሞ እንደሚኖር ይታወቃል። ቢሆንም ታላቅ እንክብካቤ ሲደረግ የሚታየው ግን ለሥጋ ብቻ ነዉ። ሥጋ እንዳትራብ፣ እዳትታመም፣ ብላም እንዳትሞት የሚደረገዉ ጥንቃቄ ከፍተኛ ነዉ። ነፍስ ግን ይመቻት አይመቻት የሚያስታዉሳት የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም።

        እዉነቱ ግን ከሥጋ በላይ ነፍስ እንዳትራብ፣ እንዳትታመምና እንዳትሞት ታላቅ እንክብካቤ የሚያስፈልጋት መሆኑ ነው። ለምን ቢባል መኖር ያለብን በእንጀራ ለሥጋችን ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃል ለነፍሳችንም ጭምር ነዉ። እስኪ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረዉ ይህንን ቃል እናስታዉሰዉ “ሰዉ የሚኖረው በእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ነው እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም” ሉቃ. 4፥4

        በሌላ በኩልም ክርስቶስ “ነፍስ ከምግብ አትበልጥምን? ሥጋስ ከልብስ አይበለጥምን?” በማለት አስተምሮናል። ማቴ 6፥25። ታዲያ የሚያሳዝነዉ ብዙዎቻችን የተራበች ወይም የታመመች አልያም ደግሞ የሞተች ነፍስ ተሸክመን ነዉ የምንኖረዉ። ምናልባት መሞት ማለትም መቃብር መግባት ብቻ የሚመስለን ከሆነ ተሣስተናል። ምክንያቱም ቆሞ መሞትም አለና። ይህንን ሓሳብ የሚያጎላልን ከመጽሓፍ ቅዱስ አንድ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ለአንዱ “ተከተለኝ” ሲለዉ እርሱም “ጌታ ሆይ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ” አለዉ። ኢየሱስ ክርስቶስም “ሙታኖቻቸዉን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዋቸዉ” በማለት ነበር መልስ የሰጠዉ። ማቴ. 8፥22

        ይህ የጌታችን ምሳሌያዊ አነጋገር ትርጉም አለዉ። መቼም አንድን የሞተ ሰዉ ሌላዉ የሞተ ተነሥቶ ሊቀብረዉ አይችልም። የክርስቶስ አነጋገርም ይህን ለማለት ፈልጐ አይደለም። መልእክቱ ግልጽ ነዉ። “ተከተለኝ” ሲለው የሕይወት ቃል ተመግቦ ነፍሱ ከሞት እንዲያድናት ነዉ። “ሙታኖቻቸዉን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዋቸዉ” ሲለው ደግሞ ለሞተ አባትህ እነዚህ ከእግዚአብሔር ቃል ርቀዉ የሚኖሩ ሰዎች እነርሱ ይቅበሩት ማለቱ ነዉ። እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን የእግዚአብሔርን ቃል ሳይመገቡ (ከእግዚአብሔር ቃል ርቀዉ የሚኖሩትን) ክርስቶስ ሙታን አላቸዉ። በእርግጥ እነዚህ ሰዎች መቃብር የወረዱ ሙታን አልነበሩም። ነገር ግን ነፍሳቸዉ የምትፈልገዉን አጥታ በነፍሳቸዉ በቁም የሞቱ ስለነበሩ ምንም እንኳ በሥጋ ቢንቀሳቀሱ ክርስቶስ ግን ሙታን አላቸዉ።

        አዎ! ሰዉ በሕይወት አለ ሊባል የሚችለዉ ነፍሱን ዕለት ዕለት የእግዚአብሔር ቃል እየመገባት መኖር ሲችል ብቻ ነዉ። ልክ ከግንድ ያልተጣበቀ ቅርንጫፍ ፍሬ እንደማይሰጥ ሁሉ ነፍስም ከፈጣሪዋ ተጣብቃ የነፍስ ምግብ ካልተመገበች መድረቋ አይቀርም። ምንም እንኳን ሥጋችን በልታና ጠጥታ ያሸበረቀ ልብስ ለብሳ ብታምር ይህን ነገር ግን ነፍስን ሊያሳምራት አይችልም። ነፍሳችን ከእግዚአብሔር ጋር ያላት ግንኙነት ካላማረ ነገር ሁሉ የተበላሸ እንጂ ያማረ አይሆንም። ምናልባት ውስጣዊ ነፍሳችንን ጎድተን ዉጫዊ አካላችንን አሳምረን ብንቀሳቀስ መልካም ያለን ሆኖ የሚሰማን ከሆነ ሞኝነት ነዉ። ምክንያቱም ክርስቶስ በወንጌሉ እንዲህ ይለናል “በውጫቸው አምረዉ የሚታዩ በውስጣቸው ግን የሙታን አጥንትንና ርኵሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን የምትመስሉ ወዮላችሁ” ማቴ. 23፥27

        በመሆኑም የነፍሳችንን ድክመት እንድናዉቅና አዉቀነው መፍትሔ ለማግኘት ይህ “ሰላማ መንፈሳዊ ላቦራቶሪ” /የምክር አገልግሎት/ ታላቅ አስተዋጽኦ አለዉ። ብዙዎች በዚሁ መንፈሳዊ ላቦራቶሪ የምክር አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ለችግራቸዉ መፍትሔ አግኝተውበታል። እርስዎም በተለያዩ ምክንያቶች ተቸግረዉ በጭንቅ የሚኖሩ ከሆኑ ከጭንቀትዎ ተላቅቀዉ ሰላምና ዕረፍት ለማግኘት የ “ሰላማ መንፈሳዊ ላቦራቶሪ” የምክር አገልግሎት አሁኑኑ ተጠቃሚ ይሁኑ። ምክንያቱም ሥጋ ከበረታችና ነፍሳችን ከተዳከመች መጨነቃችን የግድ ነዉ። ምንጊዜም የጭንቀት መንስኤ የነፍስ መዳከም ነዉና። እንዲሁም ነፍስ ከበረታችና የምትፈለገዉን አግኝታ ከበሽታዋ ከተፈወሰች ደግሞ ሰላምና ዕረፍት ማግኘታችን የማያጠራጥር ነዉ።

        እንግዲህ በዚህ “ሰላማ መንፈሳዊ ላቦራቶሪ” የምክር አገልግሎት አባል ለመሆን የምትፈልጉ የመመዝገቢያ ቅፅ (Registration form) በመሙላት ተመዝገቡ። ከዚያ በኋላ በስልክ፣ በስካይፒ አልያም በኤሜይል ወዘተ. አድራሻዬ በመገናኘት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለጥያቄዎቻችሁ መልስና መፍትሔ ታገኙበታላችሁ ብዬ አምናለሁ።

አድራሻ

ስልክ ቁጥር   ፦ +251979408418
ኤሜይል     ፦ abagebremedhnzeselama26@gmail.com
ስካይፒ      ፦ tesfa26

      መንፈሳዊ ላቦራቶሪ መጠቀም ከፈለጉ ይመዝገቡ!

©     Aba Gebremedhn Zeselama 2009 E.c