Cinque Terre

ዌብ ሳይቱ /ድህረ ገፁ/ በምን ዙርያ አገልግሎት ይሰጣል?

        በዚህ ድህረ ገፅ የጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክነቱ ክብርና የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋ፣ ክብሯና አማላጅነቷ በሰፊው ይገለጽበታል። እንደዚሁም የቅዱሳን መላእክት፣ የቅዱሳን ጻድቃን፣ የቅድስት ቤተ-ክርስቲያንና የቅዱስ ታቦት ክብር ወዘተ. የሚገለፅበት ድህረ ገፅ ነው። ይኸውም ክብራቸው እንደሚከተለው አሳጥሮ ማየት ይቻላል።

የጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ፈራጅነቱ

        ኢየሱስ ከርስቶስ አማላጅ ሳይሆን ተማላጅ ፈራጅ አምላክ ነው። ወልደ አብ ወልደ ማርያም አምላካችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጀመሪያው እግዚአብሔር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ዮሐ. 1፥1 ይለናል።

        አዎ! ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ከርስቶስ ሥጋና መለኮት ተዋህዶ የመጣ ኣምላክ ነው። ምክንያቱም ያለ እርሱ አንዳች የሆነ ነገር የለም። አምላካችን ሁሉም ገንዘቡ የሆነ እፍ ብሎ እስትንፋስ የሰጠ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን ዓለምን አሳልፎ የሚገዛ ፈጣሪ ነው። “ሁሉም በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም ሁሉ አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች” ዮሐ. 1፥3-4

        መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ምንም አንኳን በትውልድ ኢየሱስ ክርስቶስን ቀድሞት ቢወለድም ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክነቱ ቀድሞት እንደ ነበረ ከእርሱ ይልቅ እንደሚበረታና የተከበረ መሆኑን በትህትና መስክሯል። “እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፣ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል” ማቴ. 3፥11

        ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት የተነበዩ ነቢያትም ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የሚወለደው ሕፃን (ኢየሱስ ክርስቶስ) “አምላክ” መሆኑን ገና ከመወለዱ በፊት አስቀድመው በግልፅ አስቀምጠውታል። “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” ኢሳ. 9፥6

        ስለዚህ አብ ፈጣሪ ወልድ ክርስቶስ ደግሞ እንደ ፍጡር ኣድርጎ እንኳን ሊነገር ሊታሰብም አይገባም። ከሊቃውንት አባቶቻችን ስር ተቀምጠን ምሥጢረ ሥላሴ አመሣጥረን መማር ያስፈልገናል። አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሰራፂ ስላልን የሚበላለጡ አይደለም። ሦስት አማልክት አይባሉም አንድ ናቸውና። በመለኮት፣ በስልጣን፣ በአገዛዝ፣ በባህርይ፣ በህልውና በፈቃድ አንድ ይሆናሉ። ስለዚ ባለመለያየት አምላክነታቸውን መቀበል ይገባናል። “እኔና አብ አንድ ነን” ዮሓ 10፥30

        ከቅዱሳን ሓዋርያት አንዱ ቅዱስ ፊሊጶስ አብን ሌላ ክርሰቶስም ሌላ አድርጎ በማሰቡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲህ ብሎ ጠይቆት ነበር። “ፊሊጶስ፦ ጌታ ሆይ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው” ዮሐ. 14፥8። ታዲያ አምላካችንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን አስገራሚ መልስ ደግሞ እንመልከተው “ኢየሱስም አለው አንተ ፊሊጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብን በእኔ እንዳለ አታምንም?” ዮሐ. 14፥9-10

        አዎ! አለማመን ከሆነ እንጂ ይህን ቀጥተኛ መልእከት ለሁላችንን ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይደለም። አምላካችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ አምላክነቱና ፈራጅነቱ እንዲህ ብሎናል “እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ኦሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።” ራእ. 22፥12-13

የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብርዋንና አማላጅነቷን

        “ሰንበት ታዓብይ እምኩሉ ዕለት፣ ማርያም ትዓቢ እምኩሉ ፍጥረት” ተብሎ እንደተፃፈ ሁሉ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ ናት። ከፍጥረታት ሁሉ በክብርም በጸጋም የሚተካከላት የለም። ኪሩቤል ሱራፌል ሊያዩት የማይቻላቸውን መለኮታዊ እሳት ድንግል ማርያም ግን በማኅፀንዋ ተሸክማ በድንግልና ፀንሳ ፈጣሪዋን የወለደች እመቤት ክብሯንና ጸጋዋን ምን እንበለው? በእኛ አንደበትስ እንዴት ሊገለፅ ይችላል?

        በመጽሐፍ ቅዱስም “እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” ሉቃ. 1፥48 ብላ የተናገረች እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እኛም ትውልድ ነንና ብፅዕት፣ ክብርት፣ ቅድስትና ንጽህተ ንጹሃን ብለን ልናከብራት ይገባናል። የእናትነት ፍቅሯንና ጸጋ በረከቷን ምስጢሩን የተረዱ ቅዱሳን አባቶቻችን እንደ ቅዱስ ኤፍሬም፣ ቅዱስ ባስልዮስ፣ አባ ሕርያቆስና አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ወዘተ. የእመቤታችን ፍቅር ከአቅማቸው በላይ ሲሆንባቸው “በማሳነስ እንጂ በማብዛት አይደለም” በማለት ፍቅሯን ገልጸውታል።

        በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል እንኳ ክብሯንና ጸጋዋን አውቆ በልዩ ሰላምታ “ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት።” ሉቃ. 1፥28 አዎ! መንፈስ ቅዱስ ወደ እሷ ስለመጣና የልዑል ኃይል ስላደረባት ወንድ ሳታውቅ በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷ ክብሯና ጸጋዋ የሚተካከለው እንደሌለ በቂ ማስረጃ ነው።

        ክቡር አንባቢ! አባትህና እናትህን አክብር ያለን እግዚአብሔር እናቱን እንድንጠላለት የሚፈልግ ይመስልሃልን? ታዲያ የክርሰቶስን እናት ክብሯን አሳንሰው ልጇን እንወደዋለን የሚሉትን የዕብደት አስተሳሰብ ምን እንለዋለን? እስኪ እናስብ! ወላጅ እናቴን የጠላ እንዴት የእኔ ወዳጅ ሊሆን ይታሰባል? ፈጣሪዋን የወለደች ድንግል ማርያም ወድደን ክርስቶስንም ከምንም በላይ ብናፈቅረው ፍቅራችን መልክ ይኖረዋል። ድንግል ማርያምን ከጀርባ አድርገህ “ኢየሱስ ኢየሱስ፤ ጌታ ጌታ” ማለቱ ግን የጤና አይደለም። “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።” ማቴ. 7፥21

        ለመሆኑ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንድንጠላ የሚያደርገን ማን ነው? የቀድመው እባብ ሰይጣን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ አውሬው ማደሪያውንም ሊሳደብ አፉን እንደከፈተ እናነባለን። ራእ.13፥6። “ማደሪያው” የሆነች እግዚአብሔር የቀደሳት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። “ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ።” መዝ. 45/46፥4

        እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሌለችበት ሕይወት ምን ዓይነት ሕይወት ነው? ከፍቅሯ ተለይቶና ርቆ በትዕቢት መኖርስ ምን ጥቅም አለው? በትዕቢት ተሞልተው የናቋትና ያሳደዷት አላውያን ነገሥታት ፍጻሜያቸው ምን እንደሆነ ታሪኩን አናውቀውም እንዴ? እነሱም ጠፉ መንግሥታቸውም ደግሞ ጠፋ። “ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል” ኢሳ. 60፥12። አዎ! የፍቅር እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ብናከብራት ራሳችንም እንከበራለን ባናከብራት ደግሞ መዋረዳችንና መናቃችን የማይቀር ነው “የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ” ኢሳ. 60፥14

        የእመቤታችን ፍቅር የሌለበት ጉዞ መልህቅ እንደ ሌለው መርከብ ነው። የእመቤታቸን ፍቅር የጎደለው ሕይወት ጣዕም የለውም። በኑሮአችን ሁሉ ሰላምና ፍቅር እንዲኖረን የሰላምና የፍቅር እናት ስንቃችን ትሁን። ዋሳችንና ጠበቃችንም እናድርጋት። የማይበገር ወጀብም ማዕበልም ቢገጥመን እንኳ በእመቤታችን ረዳትነት ቀዝፈነው ማለፍ እንችላለን። ስለዚህ የእመቤታችንን ፍቅር በልቦናችን ጽላት ጽፈን እናኑረው።

        ስለሆነም አባታችን ዮሴፍን “ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።” ማቴ. 1፥20። ሐዋርያው ዮሐንስም “እናትህ እነኋት” ዮሐ. 19፥27 እንደተባሉ ሁሉ እኛም ድንግል ማርያም በመስቀል ሥር ያገኘናት ብርቅ የፍቅር ስጦታችን ስለሆነች እናታችንን በክብር ወስደን እናቴ፣ አለኝታዬ፣ መከታዬ፣ ትምክህቴና አማላጄ እንበላት።

የቅዱሳን መላእክት ክብርና ተራዳኢነታቸው

        አዎ! ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ ለተልእኮ የሚፋጠኑ የእግዚአብሔር ባለሟሎች ስለሆኑ ልናከብራቸው ይገባናል። ከዚህም አልፎ ቅዱሳን መላእክት ለሰው ልጅ ጠባቂና ተራዳኢ ናቸው። ስለሆነም ጥበቃቸውና ረድኤታቸው እንዲደርሰን ልናከብራቸውም ልንፈራቸውም ይገባናል። መፅሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል” መዝ. 33/34፥7 አባታችን ነቢዩ ዳንኤልም እንዲህ ይላል፦ “ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ” ዳን. 10፥13

        ከዚህም በተጨማሪ ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጅ እንዳይጠፋ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም ምህረት የሚለምኑ ናቸው። “በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል።” ዳን. 12፥1። ስለዚህ ቅዱሳን መላእክት ከቁጣቸው ለመውጣትና ጥበቃቸውንና ረድኤታቸውን ለማግኘት ልናከብራቸው፣ ልንፈራቸው ልንሰግድላቸው ይገባናል።“ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ” ዘፍ. 19፥1

        ቅዱሳን መላእክት የሰውን ልጅ ለመርዳትና ለመጠበቅ እንቅልፍም ሆነ ዕረፍት አያውቁም። ጥበቃቸው ደግሞ ሰው ክፉ ነገርና መቅሰፍት እንዳይገጥመው ለመከላከል ነው። በምንሄድበት ሁሉ ከአደጋ ሊጠብቁን ቅዱሳን መላእክት ወደ እኛ ይታዘዛሉ። “ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሰፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። በመንገድህ ሁሉ ይጠብቅህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና” መዝ. 90/91፥10-11። አዎ! ሰው በዓይኑ ከሚያየው አደጋ ብቻ ለመከላከል ይሞክራል። ቅዱሳን መላእክት ግን በዓይን ከሚታየውና የማይታየው አደጋዎች ሁሉ ይከላከሉልናል።

        ክቡር አንባቢ! እግዚአብሔርም የሰውን ደካማነት አውቆ ጠባቂ መልአክ አድርጎለታል። ሰው ጠባቂ መልአክ ባይኖረው ኖሮ እንዴት በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ይችል ነበር። ስለሆነም በምንሄድበት መንገድ ሁሉ እግዚአብሔር ጠባቂ መልአክ አድረጎልናል። “በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወደ አዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ።” ዘጸ. 23፥20

የቅዱሳን ጻድቃን ክብርና ቃልኪዳን

        ቅዱሳን ጻድቃንን ልናከብራቸው፣ ልንቀበላቸው እግዚአብሔር ፈቃዱ ነው። ቅዱሳን ጻድቃን መቀበል እኮ አምላካችን እግዚአብሔር መቀበል ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ሲያረጋግጥልን “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል” ማቴ. 10፥40 ይለናል።

        ቅዱሳን ጻድቃን ስማቸው ጠርተን በስማቸው ጸበል ጸዲቅ /ዝክር/ አድርገን ለድሃ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብናጠጣ እንኳን ዋጋ እንደምናገኝበት በግልፅ ስማቸው እየጠራ ቃል ኪዳን ሰጥቶናል። “ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም” ማቴ. 10፥41-42። ከዚህም በተጨማሪ ቅዱሳን ብናከብራቸውና ብንለምናቸው ጸሎታቸው ይረዳናል። “የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች” ያዕ. 5፥16

        ራሳችንን ዝቅ አድርገን “እኔ ኃጢኣተኛ ነኝና አንተን አስደስተው ተጋድሏቸውን የፈጸሙትን ቅዱሳን ጻድቃንን በሰጠኃቸው ቃልኪዳን ይቅር በለኝ” ብለን ብንጸልይ ስለእነርሱ ብሎ ይቅር ይለናል። “እግዚአብሔርም በሰዶም በከተማይቱ ውስጥ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ስፍራውን ሁሉ ስለእነርሱ እምራለሁ አለ” ዘፍ. 18፥26። አባታችን አብርሃም ምናልባት በሰዶም አምሳ ጻድቃን ባይገኙ ከዚያ አሥር ቢገኙስ ብሎ ጠይቆት ነበር። ታዲያ እግዚአብሔር አብርሃምን ምን አለው “እርሱም ስለ አሥሩ አላጠፋትም አለ” ዘፍ. 18፥32

        መቼም ሰው ከሰው ይማራል። የአንዱን ሰው ሕይወት ታሪክ ለሌላኛው ብዙ ትምህርት የሚሰጥ ነው። በተለይ ደግሞ ዓለምን ንቀው ወደ ገዳም ገብተው በምናኔ የሚኖሩ ቅዱሳን የሕይወት ተጋድሎአቸው በዓለም ለሚኖር ሰው ሁሉ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው። ታዲያ ከሕይወታቸው ለመማር ገድላቸውን ማንበብና ታሪካቸው ማወቅ ደግሞ ግድ ይለናል። ምክንያቱም የቅዱሳን ገድል ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ያለውን ታሪካቸው በሙሉ እንደ መስታወት ሆኖ ያሳየናል። ቅዱሳን ጻድቃን መቼ ተወለዱ? ሁሉንም ትተው እንዴትስ ወደ ምናኔ ገቡን? በአገልጉሎት ዘመናቸውስ ምን ሥራ ሠሩ? መቼና የት ቦታ አረፉ ወ.ዘ.ተ የሚሉት ጥያቄዎችንና ሓሳቦችን እየመለስ በግልጽ ያስረዳናል።

        ቅዱሳንን በሕይወት ምሰሏቸው ተብለናል። ዕብ. 13፥7። ታዲያ እንደተባልነው ሕይወታችን የቅዱሳንን ሕይወት መስሏልን? ማንን ነው የምንመስለው? መቼም እውነት እንናገር ቢባል ለሕይወታችን አርአያና ምሳሌ የምናደርጋቸው ሌሎችን ነው። ታዋቂ የፊልም ተዋንያን፣ ዘፋኞች እንዲሁም የታወቁ ስፖርተኞች የመሳሰሉትን እንደነሱ ዝነኛ ለመሆን ዓለም የምታደርገው ጥድፊያ አሁን እያየነው ያለ አስገራሚ ተግባር ነው። ሕፃን፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ሳይቀር የእነዚህ ዝነኞች የተባሉትን ሰዎች ስማቸውንና ታሪካቸውን መናገር ይችላል። ምሳሌ አድርጉአቸው የተባልነው ቅዱሳንን ግን ስማቸውንና ታሪካቸውን ተናገሩ ብንባል ብዙዎቻችን መናገር አለመቻላችን ደግሞ በጣም ያሳዝናል። “በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” ሮሜ. 12፥2

        ስለዚህ ቅዱሳን ጻድቃንን ልናከብራቸውና የጸጋን ስግደት ልንሰግድላቸው ይገባናል።ስለ ቅዱሳን ጻድቃን ክብር ሥልጣን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይገልጽልናል “ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን” 1ኛቆሮ. 6፥2። ስለዚህ ቅዱሳን ጻድቃን ማክበር እንጂ መደፋፈር አያስፈልግም “በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ” መዝ 30/31፥18። እንግዲህ ወዳጄ የቅዱሳን ጻድቃን በረከታቸውን ለማግኘት ከሕይወታቸው ተምረን ብርሃን የሆነውን መንገዳቸውን እንከተል። “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው።” ምሳ. 4፥18

የቅድስት ቤተክርስቲያንና የቅዱስ ታቦት ክብር

        ቅድስት ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ማደሪያ ናት። ምንጊዜም ዓይኑና ልቡ የማይለይባት ዘላዓለማዊት ማደሪያው ናት። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔር ቤት ቅድስት ቤተክርስቲያንን ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ “ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ” በማለት እግዚአብሔር ተናግሮታል። 1ኛነገ. 9፥3። ኢየሱስ ክርስቶስ አምላካችን የቅድስት ቤተክርስቲያናችን ራሷና ጉልላቷም ነው። ስለሆነም በጥንቃቄ ልናከብራትም ልንጠብቃትም ግድ ይለናል። “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ላራሳችሁ ተጠንቀቁ።” ሐዋ. 20፥28

        የዋኁና ትሁቱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ቤተክርስቲያንን ገበያ አድርገው በተደፋፈሩ ጊዜ ሲቆጣ እንመለከታለን። “ቤቴ የፀሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው” ማቴ. 21፥13። ይኸውም ስለ ቤተክርስቲያን ያለውን ታላቅ ክብር ያሳየናል። ስለሆነም በየጊዜው ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት መነጋገር ያስፈልገናል። “አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮቼም ያደምጣሉ” 2ኛዜና. 7፥15

        ከዚህም በተጨማሪ የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነው ቅዱስ ታቦትም ልናከብረው ይገባናል። ታቦት በሚነግሥበት ጊዜም በክብርና በፍርሃት ልናጅበው ይገባናል። “የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃልኪዳን ታቦትና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት” ኢያ. 3፥3። አዎ! እንደ አባታችን ቅዱስ ዳዊት ለቅዱስ ታቦት ታላቅ ክብር ሰጥተን ልናከብረው ያስፈልገናል። “እስራኤል ሁሉ ሆ እያሉ፥ ቀንደ መለከትና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽልና መሰንቆም በገናም እየመቱ፥ የእግዚአብሔር የቃልኪዳን ታቦት አመጡ።” 1ኛዜና. 15፥28

        ቅዱስ ታቦትም ጽላትም ሁሉ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሥራ ነው። “ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ” ዘጸ. 32፥16። የእግዚአብሔር ሥራም ልናከብረውና ልንፈራው ይገባናል። የእግዚአብሔር ማደሪያ ቅዱስ ታቦት በፍርሃት ልንሰግድለት እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይለናል፦ “ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱንና የአሰራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግንባራቸው ተደፉ” ኢያ. 7፥6

        ባጠቃላይ ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳን ሁሉ የሚገባቸውን ክብር መስጠት ይገባናል። “መፈራት ለሚገባው መፈራትን ክብርን ለሚገባው ክብርን ስጡ” ሮሜ 13፥7። ስለሆነም ይህ ድህረ ገፅ የሁሉም ክብራቸው እንድናውቅና እንድናይ በማድረግ የተለያዩ በጎ ሥራዎች /መንፈሳዊ አገልግሎት/ የሚሰራጭበት ድህረ ገፅ ነው።

©     Aba Gebremedhn Zeselama 2009 E.c